
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሴክተር መረጃን ከመንግሥት ወደ ህዝብ፤ ከህዝብ ወደ መንግስት በማድረስ መንግስትና ህዝብን በመረጃ የሚያገናኝ ለልማትና መልካም አስተዳደር ስኬት የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያገለግል ወሳኝ ሴክተር ነው። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ፈታኝ ሁኔታዎችን ወደ ዕድል በመቀየር፣ የታላቅነት ጉዞዋን እያረጋገጠች ትገኛለች፡፡
መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ የሪፎርም ሥራዎች የሀገራችንን ስብራት እየጠገኑ ዜጎች በሀገራቸው መጻኢ ዕድል ላይ ተስፋ እንዲሰነቁ ያስቻለ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ያደረገችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ተቋቁመን ብልጽግናችንን እንድናረጋግጥ የሚያስችለንን መሠረት ጥሏል፡፡ በዲፕሎማሲው ረገድም፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅና በቀጠናዊ ትስስር ላይ የተመሰረተ የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ለማጠናከር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ያሉ ሲሆን እኛም እንደዞን የበኩላችንን ድርሻ እየተወጣን እንገኛለን፡፡
ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መመስረትን ተከትሎ የተመሰረተው ምስራቅ ጉራጌ ዞን ከተመሰረተ የሁለት ዓመት ተኩል ዕድሜ ያለው ቢሆንም ክልላችን ብሎም ዞናችንም ያጋጠሙትን ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የተቻለበት፣ በዚህ አጭር ግዜ የተሞክሮ ማዕከል መሆን የተቻለበት መላው ህዝባችንን በማስተባበር የተገኘ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል። ምስራቅ ጉራጌ ዞን ከምስረታው ጀምሮ በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስና በአደረጃጀት የማደራጀት ስራን በአንድ በኩል፤ ልማትን የማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባርን ጎን ለጎን እያስኬደ በሂደቱም ከፍተኛ ውጤትን በማሳየት በአፈፃፀም ረገድ ከነባር ዞኖች እኩል በአንዳንድ ተግባራትም የተሻለ በመፈፀም ላይ የሚገኝ ዞን ነው።
በአሁኑ ወቅት ዓለም ዛሬ በዲጂታል አብዮት እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታጀበ ፈጣን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ለውጥ ላይ ትገኛለች። ይህ የቴክኖሎጂ እድገት መረጃን በፍጥነት ለማድረስ ዕድል የፈጠረ ቢሆንም፣ የሀሰተኛ መረጃዎች (Disinformation) ሥርጭት ግን ለሀገራት ደህንነት ትልቅ ስጋት ሆኗል፡፡ጨይህ ችግር ክልላችንን ብሎም ዞናችንን እየፈተነን የሚገኝ ቢሆንም የዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ተቋማዊ አቅሙን በሰው ኃይልና በማቴሪያል በተወሰነ መልኩም ቢሆን በማደራጀት፣ ዘመናዊ የዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መረጃን ከመንግሥት ወደ ህዝብ፤ ከህዝብም ወደ መንግስት በማድረስ እንዲሁም ከሁነት ዘገባ ባሻገር የዞኑን ፀጋዎች አጉልቶ በማሳየት ዞኑን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ አካባቢ እንዲሆን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
ግባችን መንግሥት እና ሕዝብ በመረጃ እንዲጣመሩና እንዲተሳሰሩ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ደረጃውን የጠበቀ ተወዳዳሪና ተዓማኒ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥርዓትን በመገንባት የምስራቅ ጉራጌ ዞንን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም ማስተዋወቅ ነው። ይህንን ሃላፊነት ለመወጣት ስትራቴጂካዊ አመራር፣ ፈጠራ እና ፍጥነት ይጠይቃል፡፡ ሕዝባችንም ከሀሰተኛ መረጃዎችና ከከፋፋይ አጀንዳዎች ራሱን በመጠበቅ፣ በሀገረ መንግስት እና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
see more

Add new comment